የታዋቂው የልብ ቀዶ ጥገና ሐኪም የዶክተር ፍቅሩ ማሩ የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ ተከበረ

የታዋቂው የልብ ቀዶ ጥገና ሐኪም የዶክተር ፍቅሩ ማሩ የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ ተከበረ

የታዋቂው የልብ ቀዶ ጥገና ሐኪም የዶክተር ፍቅሩ ማሩ የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከበረ

የአዲስ የልብ እና የውስጥ ደዌ ሕክምና ማዕከል (Addis Cardiac and Internal Medicine Center) መስራች፣ ባለቤትና ታዋቂው የልብ ቀዶ ጥገና ሐኪም የዶክተር ፍቅሩ ማሩ አንደኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ ዕለት፣ የማዕከሉ አመራሮች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ሠራተኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የቅርብ ታካሚዎቻቸው በተገኙበት  ታስቦ ውሏል።
በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ የዶክተር ፍቅሩ ማሩ አጠቃላይ የሕይወት ታሪክና በሀገራችን የሕክምና ዘርፍ ላይ ያስመዘገቡት ታላቅ ታሪክ በሰፊው ቀርቧል። በተለይም በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ዘርፍ ቀዳሚና ወደር የለሽ አስተዋፅዖ ያበረከቱ፣ የብዙዎችን ሕይወት የታደጉ እና በሙያቸው ያሳዩት የነበረው ከፍተኛ ሰብአዊነትና ለታካሚዎቻቸው የነበራቸው ርኅራኄ በዕለቱ በዝርዝር ተነስቷል። ዶክተር ፍቅሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ልብ በመጠገን፣ ተስፋ ለቆረጡት ሁሉ የሕይወት ብርሃን በመሆን ያሳለፉት መልካም ስም፣ በታካሚዎቻቸውና በትውልድ ልብ ውስጥ ፈጽሞ የማይረሳ ደማቅ አሻራ ጥሎ ማለፉ በስሜት ተገልጿል።
ይህንን ታላቅ መታሰቢያ በማስመልከትም፣ ማዕከሉ   በዛሬው መታሰቢያ ዕለት ወደ ማዕከሉ ለመጡ ታካሚዎች በሙሉ ከካርድ ክፍያ ላይ የ30% (ሰላሳ በመቶ) ልዩ ቅናሽ አድርጓል። ይህ በጎ ተግባር የዶክተር ፍቅሩን ሕያው ራዕይ ይበልጥ ለማስቀጠልና ሁልጊዜም ቢሆን የታካሚዎችን ደኅንነት ማስቀደም ከማዕከሉ ዋና እሴቶች መካከል አንዱ መሆኑን ለማሳየት የታለመ መሆኑ ተገልጿል።
በማዕከሉ የተገኙ የሥራ ባልደረቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና የቅርብ ታካሚዎችም በዕለቱ ባስተላለፉት መልእክት፦

“ዶክተር፤ የሺዎችን ልብ የጠገኑት እጆችህ፣ የፈወስካቸው ሕሙማን እና በታላቅ ጥረት የመሰረትካቸው ተቋማት ለአንተ ዘለአለማዊ ሕያው ምስክር ናቸው” ሲሉ ለታላቁ ባለሙያ ያላቸውን ጥልቅ ክብር፣ ፍቅርና ናፍቆት ገልጸዋል።
የአዲስ የልብ እና የውስጥ ደዌ ሕክምና ማዕከል አስተዳደር፣ በዚህ ታሪካዊና ስሜታዊ ዕለት በአካል በመገኘት፣ በሃሳብም ሆነ በጸሎት ቀኑን አብረው ላሳለፉ፣ መታሰቢያውን በጋራ  ላከበሩ የሕክምና ማዕከሉ ሠራተኞች፣ ውድ ታካሚዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሙሉ የላቀና የከበረ ምስጋናውን ያቀርባል።
የታላቁ ሐኪም፣ የበጎ አድራጊውና የብዙዎች መካሪ የነበሩት የዶክተር ፍቅሩ ማሩ ነፍስ በሰላም ትረፍ! ራዕያቸውና የጀመሩት መልካም ሥራ  ሁልጊዜም ሕያው ሆኖ ይቀጥላል!

 

Share with others
Appointment Appointment Reviews Reviews